የማርቆስ ወንጌል 12
Amharic NT

1በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። 2በጊዜውም ከወይን አትክልት ፍሬ ከገበሬዎቹ እንዲቀበል አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎቹ ላከ፤ 3ይዘውም ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። 4ዳግመኛም ሌላውን ባሪያ ወደ እነርሱ ላከ እርሱንም ወግረው ራሱን አቈሰሉት አዋርደውም ሰደዱት። 5ሌላውንም ላከ፤ እርሱንም ገደሉት፥ ከሌሎችም ከብዙዎች አንዳንዱን ደበደቡ አንዳንዱንም ገደሉ። 6የሚወደው አንድ ልጅ ገና ነበረው፤ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ እርሱን ከሁሉ በኋላ ወደ እነርሱ ላከ። 7እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለው፥ ርስቱም ለኛ ይሆናል ተባባሉ። 8ይዘውም ገደሉት፥ ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ ጣሉት። 9እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋል? ይመጣል ገበሬዎቹንም ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።

10ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው። የሚለውን ይህን መጽሐፍ አላነበባችሁምን?

11

12ምሳሌውንም ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አውቀዋልና ሊይዙት ፈለጉ፥ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ትተውትም ሄዱ።

13በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ። 14መጥተውም። መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ? አሉት። 15እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ። ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ አላቸው። 16እነርሱም አመጡለት። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤ እነርሱም። የቄሣር ናት አሉት። 17ኢየሱስም መልሶ። የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። በእርሱም ተደነቁ።

18ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው ጠየቁት እንዲህም አሉት። 19መምህር ሆይ፥ ሙሴ። የአንድ ሰው ወንድም ሚስቱን ትቶ ልጅ ሳያስቀር ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። 20ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ዘር ሳያስቀር ሞተ፤ 21ሁለተኛውም አገባት፥ ዘርም ሳይተው ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ 22ሰባቱም አገቡአት፥ ዘርም አላስቀሩም። ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። 23ሰባቱ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀን ሲነሡ ከእነርሱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? 24ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ስለዚህ የምትስቱ አይደለምን? 25ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም። 26ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር። እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቍጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? 27የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። እንግዲህ እጅግ ትስታላችሁ።

28ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ። ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። 29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ። እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ 30አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። 31ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። 32ጻፊውም። መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ 33በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። 34ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ። አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።

35ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ። ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ?

36ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።

37ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።

38ሲያስተምርም እንዲህ አለ። ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ 39 40የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።

41ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ 42አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። 43ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ። እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ 44ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Mark 11
Top of Page
Top of Page