የዮሐንስ ወንጌል 12
Amharic NT

1ከፋሲካም በፊት በስድስተኛው ቀን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። 2በዚያም እራት አደረጉለት፤ ማርታም ታገለግል ነበር፤ አልዓዛር ግን ከእርሱ ጋር ከተቀመጡት አንዱ ነበረ። 3ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ። 4ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። 5ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። 6ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው። 7ኢየሱስም። ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ 8ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም አለ።

9ከአይሁድም ብዙ ሕዝብ በዚያ እንደ ነበረ አውቀው መጡ፥ ከሙታንም ያስነሣውን አልዓዛርን ደግሞ እንዲያዩ ነበረ እንጂ ስለ ኢየሱስ ብቻ አይደለም። 10የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፥ 11ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።

12በማግሥቱ ወደ በዓሉ መጥተው የነበሩ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጣ በሰሙ ጊዜ፥ 13የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ። 14አንቺ የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ። 15 16ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው። 17አልዓዛርንም ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ሲያስነሣው ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ይመሰክሩለት ነበር። 18ስለዚህ ደግሞ ሕዝቡ ይህን ምልክት እንዳደረገ ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ። 19ሰለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው። አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል ተባባሉ።

20በበዓሉም ሊሰግዱ ከወጡት አንዳንዶቹ የግሪክ ሰዎች ነበሩ፤ 21እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው። ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት። 22ፊልጶስም መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። 23ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል። የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። 24እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25ነፍሱን የሚወድ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም በዚህ ዓለም የሚጠላ ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።

27አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። 28አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም። አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። 29በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ። ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች። መልአክ ተናገረው አሉ። 30ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። 31አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ 32እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ። 33በምን ዓይነትም ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ይህን ተናገረ። 34እንግዲህ ሕዝቡ። እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንዲኖር ከሕጉ ሰምተናል፤ አንተስ የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ እንዲያስፈልገው እንዴት ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው? ብለው መለሱለት። 35ኢየሱስም። ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው። ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም። 36የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው።

37ነገር ግን ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ? ብሎ የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ በእርሱ አላመኑም። 38 39ኢሳይያስ ደግሞ። በዓይኖቻቸው እንዳያዩ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ እንዳይመለሱም፥ እኔም እንዳልፈውሳቸው፥ ዓይኖቻቸውን አሳወረ ልባቸውንም አደነደነ ብሎአልና ስለዚህ ማመን አቃታቸው። 40 41ክብሩን ስለ አየ ኢሳይያስ ይህን አለ፥ ስለ እርሱም ተናገረ።

42ከዚህም ጋር ከአለቆች ደግሞ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ነገር ግን ከምኵራብ እንዳያስወጡአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም፤ 43ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና።

44ኢየሱስም ጮኸ፥ እንዲህም አለ። በእኔ የሚያምን በላከኝ ማመኑ ነው እንጂ በእኔ አይደለም፤ 45እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል። 46በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። 47ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም። 48የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል። 49እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም ትእዛዝ ሰጠኝ። 50ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

John 11
Top of Page
Top of Page