የሐዋርያት ሥራ 26
Amharic NT

1አግሪጳም ጳውሎስን። ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል አለው። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ መለሰ እንዲህ ሲል።

2ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። 3

4ከመጀመሪያ አንሥቶ በሕዝቤ መካከል በኢየሩሳሌም የሆነውን፥ ከታናሽነቴ ጀምሬ የኖርሁትን ኑሮዬን አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ 5ሊመሰክሩ ይወዱ እንደ ሆነ፥ በአምልኮአችን ከሁሉ ይልቅ ሕግን በመጠንቀቅ እንደሚተጋ ወገን ፈሪሳዊ ሆኜ እንደኖርሁ ከጥንት ጀምረው አውቀውኛልና። 6አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። 7ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ። 8እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል?

9እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር። 10ይህንም ደግሞ በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከካህናት አለቆችም ሥልጣን ተቀብዬ እኔ ከቅዱሳን ብዙዎችን በወኅኒ አሳሰርኋቸው፥ ሲገድሉአቸውም አብሬ ተቸሁ። 11በምኵራብም ሁሉ ብዙ ጊዜ እየቀጣሁ ይሰድቡት ዘንድ ግድ አልኋቸው፤ ያለ ልክ ስቈጣባቸውም እስከ ውጭ አገር ከተማዎች ድረስ እንኳ አሳድድ ነበር።

12ስለዚህም ነገ ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ስሄድ፥ 13ንጉሥ ሆይ፥ በመንገድ ሳለሁ እኩል ቀን ሲሆን በዙሪያዬና ከእኔ ጋር በሄዱት ዙሪያ ከፀሐይ ብሩህነት የበለጠ ብርሃን ከሰማይ ሲበራ አየሁ፤ 14ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል የሚል ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገረኝ ሰማሁ። 15እኔም። ጌታ ሆይ፥ ማንነህ? አልሁ። እርሱም አለኝ። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ። 16ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና። 17የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ። 18

19ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም። 20ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ። 21ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ። 22ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም። 23

24እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ። ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል አለው። 25ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ። ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአእምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም። 26በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና። 27ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ነቢያትን ታምናለህን? እንድታምናቸው አውቃለሁ። 28አግሪጳም ጳውሎስን። በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ አለው። 29ጳውሎስም። በጥቂት ቢሆን ወይም በብዙ አንተ ብቻ አይደለህም ነገር ግን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ እስራቴ በቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እለምናለሁ አለው።

30ንጉሡም አገረ ገዡም በርኒቄም ከእነርሱም ጋር ተቀምጠው የነበሩት ተነሡ፥ 31ፈቀቅ ብለውም እርስ በርሳቸው። ይህ ሰው እንኳንስ ለሞት ለእስራትም የሚገባ ምንም አላደረገ ብለው ተነጋገሩ። 32አግሪጳም ፈስጦስን። ይህ ሰው እኮ ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ይፈታ ዘንድ ይቻል ነበር አለው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Acts 25
Top of Page
Top of Page