የሐዋርያት ሥራ 20
Amharic NT

1ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፥ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ። 2ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ። 3በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሴራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ። 4የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤ 5እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን። 6እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን።

7ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ። 8ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ። 9አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። 10ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው። 11ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። 12ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ።

13እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና። 14በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤ 15በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፥ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን። 16ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።

17ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤ 18ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤ 19 20ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም። 21 22አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ በመንፈስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፥ በዚያም የሚያገኘኝ ምን እንደ ሆነ አላውቅም፤ 23ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ። እስራትና መከራ ይቆይሃል ብሎ በየከተማው ሁሉ ይመሰክርልኛል። 24ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።

25አሁንም፥ እነሆ፥ እኔ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንዳትዩ አውቃለሁ። 26ስለዚህ እኔ ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ በዚች ቀን እመሰክርላችኋለሁ። 27የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። 28በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 29ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። 30 31ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ። 32አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ። 33ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤ 34እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ። 35እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ።

36ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ። 37ሁሉም እጅግ አለቀሱ፥ ጳውሎስንም አንገቱን አቅፈው ይስሙት ነበር፤ 38ይልቁንም። ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታዩም ስላላቸው ነገር እጅግ አዘኑ። እስከ መርከብም ድረስ ሸኙት።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Acts 19
Top of Page
Top of Page