ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1
Amharic NT

1የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ 2ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

3ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። 4 5 6በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ 7በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። 8በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። 9ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። 10 11

12ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 13ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ 14በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። 15አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ 16እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ 17እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። 18ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። 19ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ 20ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል።

21ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። 22ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። 23በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ 24ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። 25ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። 26

27ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። 28በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ 29ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ 30በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Ephesians 6
Top of Page
Top of Page