የይሁዳ መልእክት 1
Amharic NT

1የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ 2ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።

3ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። 4ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።

5ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። 6መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። 7እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።

8እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ። 9የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር። ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም። 10እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ። 11ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል። 12እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ 13የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።

14ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ። እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ። 15 16እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል።

17እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤ 18እነርሱ። በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና። 19እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። 20እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ 21ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። 22አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥ 23አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።

24ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው 25ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

3 John 1
Top of Page
Top of Page