የዮሐንስ ወንጌል 16
Amharic NT

1እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። 2ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው። 4ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከእንናንተም ጋር ስለ ነበርሁ በመጀመሪያ ይህን አልነገርኋችሁም።

5አሁን ግን ወደ ላከኝ እሄዳለሁ ከእናንተም። ወዴት ትሄዳለህ? ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። 6ነገር ግን ይህን ስለ ተናገርኋችሁ ኀዘን በልባችሁ ሞልቶአል። 7እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ 9ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ 10 11ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።

12የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ። ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።

16ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና።

17ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁም፤ ደግሞ። ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። 18እንግዲህ። ጥቂት የሚለው ይህ ምንድር ነው? የሚናገረውን አናውቅም አሉ። 19ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ወደዱ አውቆ እንዲህ አላቸው። ጥቂት ጊዜ አለ፥ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፥ ታዩኛላችሁ ስላልሁ፥ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን? 20እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ ታለቅሳለችሁ ሙሾም ታወጣላችሁ፥ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችሁ፥ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራትዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ሕፃን ከወለደች በኋላ፥ ሰው በዓለም ተወልዶአልና ስለ ደስታዋ መከራዋን ኋላ አታስበውም። 22እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።

23በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። 24እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።

25ይህን በምሳሌ ነግሬአችኋለሁ፤ ነገር ግን ስለ አብ ለእናንተ በግልጥ የምናገርበት እንጂ ከዚያ ወዲያ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል። 26በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ 27እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና። 28ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ።

29ደቀ መዛሙርቱ። እነሆ፥ አሁን በግልጥ ትናገራለህ በምሳሌም ምንም አትነግርም። 30ሁሉን እንድታውቅ ማንምም ሊጠይቅህ እንዳትፈልግ አሁን እናውቃለን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን አሉት። 31ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። አሁን ታምናላችሁን? 32እነሆ፥ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፥ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። 33በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

John 15
Top of Page
Top of Page