የሉቃስ ወንጌል 16
Amharic NT

1ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ በእርሱ ዘንድ። ይህ ሰው ያለህን ይበትናል ብለው ከሰሱት። 2ጠርቶም። ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ አለው። 3መጋቢውም በልቡ። ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፥ መለመንም አፍራለሁ። 4ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ አለ። 5የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የፊተኛውን። ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ? አለው። 6እርሱም። መቶ ማድጋ ዘይት አለ። ደብዳቤህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ አምሳ ብለህ ጻፍ አለው። 7በኋላም ሌላውን። አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ? አለው። እርሱም። መቶ ጫን ስንዴ አለ። ደብዳቤህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ አለው። 8ጌታውም ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና። 9እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ።

10ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። 11እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? 12በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? 13ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።

14ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። 15እንዲህም አላቸው። ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና።

16ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ በኃይል ይገቡባታል። 17ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል።

18ሚስቱንም የሚፈታ ሁሉ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፥ ከባልዋም የተፈታችውን የሚያገባ ያመነዝራል።

19ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። 20አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ 21ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። 22ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። 23በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። 24እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። 25አብርሃም ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። 26ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ። 27እርሱም። እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ 28እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ። 29አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው። 30እርሱም። አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ። 31ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Luke 15
Top of Page
Top of Page