Amharic NT 1በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ። ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። 2በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። 3ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ። 4እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። 5ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። 6እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። 7ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል። 8በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። 9ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፥ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። 10እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። 11ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ፥ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። 12በሰማይም። ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። 13በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፥ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፥ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፥ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። 14ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል። 15ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም። የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል 16የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው 17ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ። ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤ 18አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ። 19በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ። Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia! Bible Hub |