የዮሐንስ ራእይ 20
Amharic NT

1የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ። 2የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፥ 3ሺህ ዓመትም አሰረው፥ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።

4ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ። 5የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው። 6በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።

7ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥ 8በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው። 9ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው። 10ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።

11ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም። 12ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። 13ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። 14ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። 15በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።

Revised Amharic Bible in XML (2003). Printed version by United Bible Societies (C)1962. E-Text in transliterated ASCII format by Lapsley/Brooks Foundation 1994. Unicode UTF-8 transformation and XML-tagging by Dirk Röckmann 2003 (www.nt-text.net). -- With kind permission of the Bible Society of Ethiopia. Every non-commercial work using this data in any form must fully include this copyright statement! Every commercial use of parts or the complete data in any form needs written permission of the Bible Society of Ethiopia!

Bible Hub

Revelation 19
Top of Page
Top of Page